የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞች ግንኙነት ማዕከሉን አገልግሎት ማሻሻል የሚያስችል ፕሮጀክት ተግባር ላይ አዋለ።

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብይ ጌታቸው ባንኩ በ951፣ በ847 እና በ915 አጭር የጥሪ መስመሮች ደንበኞቹን የሚያስተናግደበት አቫያ የተሰኘ አዲስና የዘመነ ስርዓት በጥሪ ማዕከሉ ላይ ተግባራዊ ማድረጉን አስታውቀዋል። የሲቢኢ ብር ደንበኞች በ847 አጭር የጥሪ መስመር ላይ በመደወል ለብቻ እንዲስተናገዱ በአዲስ መልክ መዘጋጀቱንና ፖስ ማሽን የሚያስጠቅሙ ኮርፖሬት ደንበኞች ደግሞ በ915 አጭር የጥሪ መስመር ላይ በመደወል እንዲስተናገዱ መዘጋጀቱንም አቶ አብይ ገልፀዋል። በተጨማሪም በባንኩ ዌብሳይት https://combanketh.et/፣ የሞባይል እና የሲቢኢ ብር መተግበሪያዎች እንዲሁም የማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ በቻትቦት አማካኝነት የደንበኞችን ጥያቄ ማስተናገድ የሚያስችል ፕሮጀክት እንደሆነ ተናግረዋል። ስርዓቱ ደንበኞች የጥሪ ማዕከሉን ሠራተኞች እገዛ ሳያሻቸው ከባንኩ የሚያገኙትን አገልግሎቶች በራስ አገዝ አገልግሎት ማግኘት እንደሚያስችላቸው ይህም የጥሪ ማዕከሉ ላይ የሚኖረውን ጫና ይቀንሳል ተብሏል። ባንኩ ከዚህ ቀደም ይጠቀምበት የነበረው ስርዓት እየጨመረ ያለውን የደንበኞች ቁጥር ለማስተናገድ በቂ እንዳልነበር አቶ አብይ አስታውሰው በአዲሱ ፕሮጀክት ይህን ታሳቢ በማድረግ ችግሩ እንደሚፈታ ገልፀዋል። የቻት ቦት አገልግሎቱ በቅርቡ አገልግሎት የሚጀምር ሲሆን የድምፅ ጥሪ አገልግሎቶቹ በ951፣ በ915 እና በ847 አጭር የጥሪ መስመሮች አማካኝነት በአዲስ መልክ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁሌም የሚተማመኑበት ባንክ!